በመጪዎቹ አሥር ቀናት ለክረምት ዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ኢንስቲትዩቱ በላከው መግለጫ፤ በመጪዎቹ አሥር ቀናት ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል ብሏል።
በዚህም በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች የተሻለ ጥንካሬ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቁሟል።
እርጥበታማው የአየር ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በመጠንና በሥርጭት እንደሚስፋፋና ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ እንደሚኖራቸውም አመላክቷል።
በመካከለኛው፣ ሰሜን፣ ምስራቅ እና በደቡብ የሀገራችን አካባቢዎች ደግሞ ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ገልጿል።
በመጪዎቹ ቀናት በሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ምክንያት፣ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ጠቁሟል።
አልፎ አልፎ በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በመነሳት፤ በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ እንደሚያገኙም ተመልክቷል።
ስለሆነም በእነዚህ ቀናት የሚኖረውን የዝናብ መጠንና ስርጭት በአግባቡ በመጠቀምና በማሰባሰብ፣ በዚህ ወቅት የሚካሄዱ የግብርና እንቅስቃሴ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
በእነዚህ አስር ቀናት በሚኖረው ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል ምክንያት በአፋር ክልል፣ በሰሜን ምስራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የቀኑ ሙቀት ከፍተኛ እንደሚሆን አሃዛዊ ትንበያዎች አመላክተዋል።
በመጪዎቹ አስር ቀናት የደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ የሰሜን ምዕራብ፣ የሰሜን እና የመካከለኛው የመኸር እና የበልግ ሰብል አብቃይ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
የሚኖረውን መልካም አጋጣሚ በተሟላ መልኩ በመጠቀምና አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሃሳብን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
በእነዚህ ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው የገፀ-ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
በመሆኑም የሚኖረውን መልካም አጋጣሚ በተሟላ መልኩ በመጠቀምና የሚጠበቁ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በመቀነስ፣ የውሃ ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሃሳብን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
በቴሌግራም ይቀላቀሉ
👇🏽👇🏽👇🏽👇🏽👇🏽
https://t.me/utopiatowday
Subscribe to get the latest posts sent to your email.
