የሀገር አቀፉ ምርጫ 2018 ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ከኢዜማ የተሠጠ መግለጫ !!
ሀገር አቀፉ ምርጫ 2018 መጠናቀቁን በትላንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ የምርጫ ውጤት በማሣወቅ አረጋግጧል፤ ምርጫው ከነእንከኖቹም ቢሆን በሰላም በመጠናቀቁ ፓርቲያችን እንኳን ደስ አለን ለማለት ይወዳል።
በተጨማሪም ፓርቲያችን ለውድድር በቀረበባቸው ቦታዎች 13 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 73 የክልል እና የከተማ ምክር ቤት ወንበሮችን በድምሩ 86 መቀመጫዎችን በማግኘት በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚው ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ አጠናቋል። ይህንን ተጨባጭ ስኬት ላስመዘገቡ የፓርቲያችን ዕጩዎች፣ አባላት፣ ደጋፊዎች እና በሂደቱ በቅንነት ለተሳተፉ አካላት ሁሉ እንኳን ደስ አለን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል።
ፓርቲያችን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ባሉት ዓመታት ጠንካራ ጎኖቹን በማስቀጠል እንዲሁም የነበሩበትን ክፍተቶች በስትራቴጂ እና ሌሎች አስፈላጊ ተግባራት በመሙላት ተጨባጭ የተፎካካሪ ፓርቲነት ሚናውን ጊዜ ሳያባክን የሚጀምረው ዛሬ መሆኑን እየገለፅን፤ በነዚህ ዓመታት ከዚህ ቀደም ስናደርገው እንደነበረ ሁሉ ብሔራዊ ጥቅሞችን በሚያሣኩ ጉዳዮች ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃይል ጋር በመተባበር የምንንቀሳቀስበት መፎካከሪያ አጀንዳዎች ላይ ማኅበረሰባችንን በሚመጥን ጨዋነት ልዩነቶቻችንን እና ትችቶቻችንን እያቀረብን የጀመርነውን ጤናማና ዘመናዊ የፖለቲካ ባሕል የማዋለድ ተግባራችንን በተጠናከረ መልኩ የምንቀጥልበት እንዲሁም ለተጨማሪ ስኬት የምንንደረደርበት እንደሚሆን ቃል እንገባለን።
በመጨረሻም ገዢ ሆኖ እንዲቀጥል ለተመረጠው ብልጽግና ፓርቲ እንዲሁም በውድድሩ ተሳትፋችሁ የሕዝብ ውክልናን ላሳካችሁ ተፎካካሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እንወዳለን።
አሸናፊው ፓርቲ ከዛሬ ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባትና ፍትሐዊ የፖለቲካ ምህዳርን ለሁሉም እኩል ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንዲሠራ፤ ለሀገር እድገትና ለውጥ ጠቃሚ ሀሳቦች ከማንኛውም ወገን ሊገኙ እንደሚችሉ በመረዳት አማራጭ ሃሳቦችን እንዲሰማ፤ እንዲሁም ትችቶችን በሆደ ሰፊነት እያስተናገደ ሀገራችን የሚያስፈልጋትን ዴሞክራሲ በጋራ እንድንገነባ ጥሪ እናቀርባለን።
ኢዜማ
በቴሌግራም ይቀላቀሉ
👇🏽👇🏽👇🏽👇🏽👇🏽
https://t.me/utopiatowday
Subscribe to get the latest posts sent to your email.
