ተራማጆቹ ከበደ ሚካኤል ፣ ግርማሜ ንዋይ ፣ አሰፋ ገብረማርያም እና ሚሊዮን ነቅንቅ
አሰፋ በ1949ዓም በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ በትምህርት ሥርዓት ክፍል ውስጥ መስራት ጀመረ።
በእዚያ በጊዜው ተራማጅ ዲሞክራቶች ብሎ የሚጠራቸውን ብዙ ሰዎች አገኘ። ለይቶ ከጠቀሳቸው መሐል የትምህርት ስርአት ክፍል ዋና ኃላፊና የአሰፋ አለቃ የነበረው ሚሊዮን ነቅንቅ፣ ከሲዳሞ ድረስ እነሚሊዮንን ለመጠየቅ የሚመጣው የ1953ቱ የመፈንቅለ መንግስት የርዕዮተ አለም መሪ የነበረው ግርማሜ ነዋይ ይገኙበታል።
በወቅቱ ከበደ ሚካኤል የትምህርት ሚኒስትር ዋና ዳይሬክተር እና የሚሊዮን አለቃ ሲሆኑ፣ አሰፋ “በቅርብም ባይሆን” ያውቃቸው ነበር። ሚሊዮን ነቅንቅ ራሱ ገጣሚ ነበር፤እንደውም “ሮሚዮ እና ዡልየት”ን ከከበደ ሚካኤል በፊት “ካለቁ ታረቁ” በሚል ርዕስ ተርጉሟል።
አሰፋንም ያበረታታው ነበር ፤ በዚህ መሰረት የአሰፋን የ”ጁሊየስ ቄሳር” ትርጉም ስህተቱን አርሞ ለማተሚያ ቤት ዝግጁ አድርጎለታል። ሚሊዮን አማርኛን በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማሪያ ቋንቋ እንዲሆን በማድረግ የመጀመሪያው የትምህርት ስርዓት ኃላፊ ነበር።
አሰፋ በዚህ ወቅት የተዋወቃቸው ዲሞክራቶች ተጽእኖ እየፈጠሩበት እንዲሁም፣ለወደፊቱ ሙያዊ ሕይወቱ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነበር።
የብሪታኒያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለመግባት የሚያስፈልገው አንድ ውይም ሁለት የA ደረጃፈተናዎችን ማለፍ ነው። በዝነኛው የለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብቶ ኢኮኖሚክስ ወይም ስታትስቲክስ ማጥናት ይፈልጋል። ስለዚህ በሒሳብ እና ስታትስቲክስ ጎበዝ ስለሆነ፣ ሒሳብ እና ኢኮኖሚክስ በA ደረጃ፣ በርቀት ትምህርት መውሰድ ጀመረ።
ጊዜው ኢትዮጵያ በታላቅ ተስፋ የተሞላችበት ጊዜ ነበር። ንጉሡ የብር ኢዮቤልዩ በዓላቸውን በ1948 ሲያከብሩ፣ የ1923 ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተደርጎበት አዲስ ሕገ መንግሥት አስረቅቀዋል።
ይህ አዲስ ሕገ መንግሥት የፕሬስ ነፃነት፣ የንግግር ነፃነት እና ሌሎችም ደስ ደስ የሚሉ ሀሳቦችን ይዟል። “ሁሉም ሰው የሚያወራው ስለዚህ ነበር”፤እነሆ በመጨረሻ “ያለ ሳንሱር” መናገር፣ መጻፍ እና ማተም ሊችሉ ነው። ስለዚህ አሰፋ “የጁልየስ ቄሳር” ትርጉሙን ለህትመት አዘጋጀና ወደ ተስፋ ገብረስላሴ ማተሚያ ቤት ይዞት ሄደ።
በጊዜው በኢትዮጵያ የሚታተሙ መጼሕፍት በፊት ገፃቸው የንጉሡን ምስል መያዛቸው ደንብ ነበር።አሰፋ ግን ከዚህ ደንብ ወጥቶ፣ የንጉሡን ተወዳጅ ልጅ የሀረሩን መስፍን የልኡል መኮንንን ምስል በምትኩ አስገባ። ልዑሉም የሞቱት በዚሁ ዓመት ነበር።
አሰፋ መጽሐፉ በሙሉ ከመታተሙ በፊት ነበር ይህን ያደረገው።በተጨማሪ መኳንንቱ ላይ በምፀት የሚያፌዝ ግጥም ጣል አድርጎ ነበር ፤ ነገር ግን ድብቅ ስለሆነ ማንም አይደርስበትም።
አሳታሚዎች ጋር እየሄደ የተስተካከሉትን ቅጂዎች ያነብ ነበር።የመጨረሻው ትእይንት ሲታተም ሳንሱር አድራጊዎቹ እየፈለጉት እንደነበር ሰማ። የንጉሡን ፎቶ ሳያስገባ መጽሐፍ ለማተም መሞከር “ከደንብ ውጪ” መሆኑን ሳንሱረኞቹ ነገሩት። በየቦታው “ሰላዮችና ጆሮ ጠቢዎች” ስለነበሯቸው፣ በማተሚያ ቤት ውስጥ የሚሰራ አንድ ሰው “የንጉሱ ፎቶ መቅረቱን” ነግሯቸው መሆን አለበት።
ኢትዮጵያ ግዛት ስለሆነች፣ንጉሠ ነገሥቷ በዚህ ዐይነት መንገድ “መሞት” እንደሌለበት ተነገረው።
ስለዚህ መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ሳይከፋፈል እንዲወረስ ተደረገ።
አሰፋ ጥቂት ቅጂዎች ብቻ ደርሰውታል። በጊዜው ደራሲዎች ለአታሚዎች በቅድሚያ መክፈላቸው እንደ ህግ ነበር። ነገር ግን የአሰፋ ጓደኞች በጊዜው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪ የነበረውን የአታሚውን ልጅ ያውቁት ነበር። አሰፋ እና ልጁ ከተዋወቁ በኋላ በሱ በኩል ለህትመት በቅድሚያ ሳይከፍል መጽሐፉ መታተም ቻለ። ስለዚህ አሰፋ ሰባራ ሳንቲም አልከሰረም።
የኃይለሥላሴ “የፕሬስ ነፃነት” እዚህ ድረስ ነበር ይላል አሰፋ። ሰዎች ግን እስከ 1953ቱ መፈንቅለ መንግስት ድረስ ሳንሱሩ የላላ ነበር ፤ ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ ግን ዳግም ጠበቀ ይላሉ።
በዚህ መጥፎ አጋጣሚ የተነሳ፣ ይህ መጽሐፍ የስራ መስኩን ሙሉ ለሙሉ እንዳስለወጠው አሰፋ ይናገራል።ተስፋ መቁረጥ ስለወረሰው፣ ብዙም ሳይቆይ ስራውን ለቀቀ።
በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እሳቸውን ሳያማክራቸው ከከበደ ሚካኤል ስራዎች ላይ ቀንጭቦ የጠቀሰው ጥቅስ ስለነበረ፣ ስማቸውን በመጥቀሱ ብቻ ለሳቸውም ችግር ፈጠረባቸው።
ምናልባትም ሳንሱረኞቹ ከበደ ሚካኤል ስለጉዳዩ ቅድሚያ ሳያውቁ አይቀርም የሚል ጥርጣሬ ሳያድርባቸው አልቀረም። አሰፋ የA ደረጃ ፈተናውን ካለፈ ከበደ ወደ ለንደን ዩኒቨርስቲ እንደሚልኩት ቃል ገብተው ነበር። አሁን ግን ቃላቸውን በማጠፋቸው፣አሰፋን ለተጨማሪ ብስጭት ዳረገው።
አሰፋ ከትምህርት ሚኒስቴር ከለቀቀ በኋላ፣ወደ ጅማ ሄዶ በጅማ ሁለተኛ ደረጃ የእርሻ ትምህርት ቤት ማስተማር ጀመረ። ትምህርት ቤቱ የሚተዳደረው በአሜሪካኖችና በእርሻ ሚኒስቴር ትብብር ነው። ይህ አጋጣሚ አሰፋ ከአዲስ አበባ ውጪ ለረዥም ጊዜ የቆየበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነበር። በ1949 መጨረሻ አካባቢ ወደ ጅማ የሄደ፣ የመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ ሊደረግ ትንሽ ጊዜ እስኪ ቀረው ድረስ ቆይቷል። ጥቅምት 1953 በዴሞክራት ጓደኞቹ ሚሊዮን ነቅንቅ እና ታደሰ ተፈራ እርዳታ፣ ዳግመኛ ትምህርት ሚኒስቴርን ተቀላቀለ ።
ጥቋቁር አናብስት ፣ ተርጓሚ ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው እና ኤፍሬም ጀማል አብዱ ፣ ገጽ 279 -281
በቴሌግራም ይቀላቀሉ
👇👇👇👇👇👇
https://t.me/utopiatowday
Subscribe to get the latest posts sent to your email.
